“አዎን አማራ ነኝ”!
(ለፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ)
እሚያነጋግረን ብዙ እሚያስጨንቀን
ሌላ ተግባር ጠፍቶ ባገር እሚከወን፣
የዕድገት ደረጃችን የደረስንበቱ
መሸንሸን ከሆነ ዝርያን ባይነቱ፣
ተፈጥሮ ያደለችኝ
መርቃ የሰጠችኝ፣
ከሥር መሰረቱ
ከጠዋት ከጥንቱ፣
ያዳም የሔዋን ዘር ህልውና ያለኝ
በኔነቴ እማምን አዎን አማራ ነኝ!
የዋህ ሆደ-ቡቡ ሁሉን አሳዳሪ
ከሁሉ አዳሪ
ልበ-ሙሉ ቆራጥ በቁም-ነገር ኗሪ፣
በራሴ እምታመን ባገሬ እመኮራ
ለሃቅ እመታገል ላገሬ እምሠራ፣
ሸፍጥና ክህደት ባንዳነት ያልነካኝ
የነፃሁ የጠራሁ አዎን አማራ ነኝ!
የሀገሬን ክብር ታሪኬን እማልሸጥ
ዘመድ ወገኖቼን በብር እማልለውጥ፣
እማልንበረከክ ለነጭ ፍርፋሪ
ጎጠኛ ያይደለሁ ትውልድ አሳፋሪ፣
ጀግንነት አመሌ ወኔ ያልተለየኝ
ተጠየቅ ካላችሁ አዎን አማራ ነኝ!
የዘመኑ “ጥበብ” የኛ መታወቂያ
ከሆነ መለያው የዘር-ግንድ መጠሪያ፣
በኢትዮጵያዊነቴ በኔነቴ የጸናሁ፣
አዎን አማራ ነኝ! የኮራሁ የደራሁ።
ጌታቸው አበራ
ነሐሴ ፲፱፻፹፭ ዓ/ም
(ኦገስት 1993)
